ሱዳናውያን ወታደራዊ መንግስታቸውን መቃወማቸውን ቀጥለዋል

ሱዳናውያን ወታደራዊ መንግስታቸውን በመቃዎም አሁንም ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን ቀጥለዋል፡፡

ባለፈው አመት የተካሄደውን መፈንቅለ መንግስት በመቃወም በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን በካርቱም ፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግስት ፊት ለፊት ባደረጉት ሰልፍ አንድ ሱዳናዊ ተቃዋሚ በጥይት ተመትቶ መሞቱን የህክምና ባለሙያዎች ተናግረዋል።

ጄኔራል አብዱልፈታህ አል-ቡርሃን ባለፈው አመት ጥቅምት 25 ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ካደረጉ በኋላ በተደረጉ የተቃውሞ ሰለማዊ ሰልፎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር 84 መድረሱን ገለልተኛ የህክምና ባለሙያዎች ቡድን አስታውቋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰባዊ መብት ባለሙያ የሆኑት አዳማ ዲንግ ወደ ሱዳን በሄዱበት ወቅት የሱዳን ባለሥልጣናት በተቃዋሚዎች ላይ የሚወስዷቸው እርምጃዎች እንዳሳሰባቸው ገልፀዋል፡፡

የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም በተመሳሳይ የሱዳን ተቃዋሚዎች ጉዳይ እንደሚያሳስበው የገለፀ ሲሆን ሁከቱ በዚህ የሚቀጥል ከሆነ ተጨማሪ መዘዞች ሊመጡ እንደሚችሉ ያለውን ስጋት ገልጿል፡፡

የሱዳን የቅርብ ጊዜ መፈንቅለ መንግሥቱ ሰፊ ዓለም አቀፍ ውግዘት እያጋጠመው ሲሆን ሀገሪቱ ያላት ዲፕሎማሲየዊ ግንኙነት እንዲቀዛቀዝ ምክንያት መሆኑን አፍሪካ ኒውስ በዘገባው አስታውቋል፡፡ (ኤፍ ቢሲ)

የዓድዋ በአልን ምክንያት በማድረግ 21 ጊዜ መድፍ ይተኮሳል

የካቲት 23 ቀን 2014 ዓ.ም የሚከበረውን የዓድዋ በአዓል ምክንያት በማድረግ 21 ጊዜ መድፍ ይተኮሳል፡፡

በዕለቱ ከማለዳው 12፡00 ሰአት 21 ጊዜ መድፍ እንደሚተኮስ የመከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።(ኤፍ ቢ ሲ)

የሩሲያ እና ዩክሬን የሰላም ድርድር ዛሬ በቤላሩስ ይጀመራል
የሩሲያ እና ዩክሬን የሰላም ድርድር በዛሬው እለት በቤላሩስ እንደሚጀምር ተገልጿል፡፡
በቤላሩስ የሚደረገው የሁለቱ አገራት የሰላም ድርድር በዩክሬን የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻን ለማስቆም ያለመ ስለመሆኑ ተመላክቷል፡፡

ብዙ የሩሲያ ቋንቋ ተናጋሪዎች ያሏቸውን የዶኔትስክ እና የሉጋንስክ ግዛቶችን ከጸረ-ሩሲያውያን ለመጠበቅ በሚል ሞስኮ በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረች ዛሬ ስድስተኛ ቀኑን ይዟል፡፡

ከወታደራዊ ዘመቻው ጥቂት ቀናት በኋላ የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ÷ አገራቸው ከሩሲያጋር ለመወያየት ዝግጁ መሆኗን ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም የሚደረገው ድርድር በአገራቱ መካከል የተጀመረውን ጦርነት ማስቆም ያስችላል በሚል በተስፋ ሲጠበቅ ቆይቷል፡፡

እንደ አር ቲ ዘገባ አገራቱ በዛሬው ዕለት የሰላም ድርድሩን የሚጀምሩ ሲሆን÷ ምክክሩም ከዩክሬን ድንበር አቅራቢያ በምትገኘው ቤላሩስ ከሰዓታት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የቤላሩስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የአገራቱን የሰላም ድርድር ለማስጀመር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጓን አስታውቋል::(ኤፍ ቢ ሲ)

"የአድዋን ታሪክ በሚገባ በመለየት አሁን ላለንበት ችግር መፍቻ ቁልፍ ማድረግ ይገባል" - ሂሩት ካሳው (ዶክተር)

የአድዋን ታሪክ በሚገባ በመለየት አሁን ላለንበት ችግር መፍቻ ቁልፍ ማድረግ ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህል ኪነጥበባትና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶክተር) ገለጹ።

የአድዋ ድል በዓል ለ126ኛ ጊዜ “አድዋን ለኢትዮጵያውያን ኅብረት፣ ለአፍሪካ የነፃነት ጮራ” በሚል መሪ ሃሳብ የሚከበረውን በአል አስመልክቶ የውይይት መድረክ እየተካሄደ ነው።

በዚህ መድርክ ላይ የቢሮዉ ሃላፊው እንደገለጹት፣ አድዋ የነጻነት ድል ብቻ ሳይሆን ፍትህ፣ አርነት፣ ሉአላዊነት የተገኘበት ድል ነው። ይህን በተለየ መንገድ ማየት መጠቀም ያስፈልጋል።

እንደ ዶክተር ሂሩት ንግግር፣ አድዋ ኢትዮጵያ ለአለም ፍትህን ያሳየችበትና በአለም እይታ ውስጥ የገባችበት ድል ነው።

ስለዚህ አድዋን በሚገባ በመረዳት አሁን ላለንበት ችግር የመፍቻ ቁልፍ አድርጐ መጠቀም ያስፈልጋል።
በፓናል ውይይቱ ከአድዋ ምን መማር አለብን፣ ከአድዋ በኋላ ኢትዮጵያ ምን አገኘች፣ ምን ሆነች የሚሉ ጉዳዮችን በጥናታዊ ጹሁፍ ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል።

በውይይቱ አባትና እናት አርበኞች፣ የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተወካዮችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ተገኝተዋል።(ኢ.ፕ.ድ)

የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ዛሬ ተጀምሯል

ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ዛሬ በጀመረው ስብሰባው በወሳኝ አገራዊ አጀንዳዎችና የፓርቲ ሥራዎች ላይ ተወያይቶ በቀጣይ ስለሚከናወኑ ተግባራት አቅጣጫ ያስቀምጣል ተብሎ እንደሚጠበቅ የብልጽግና ፓርቲ ዋና ጽ/ቤት አስታውቋል። (ኢዜአ)

በአፋር የተከፈተው ጥቃት የኢትዮጵያን ገጽታ ለማጠልሸት ያለመ ነው₋ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

ሰሞኑን በአሸባሪው ህወሃት በአፋር የተከፈተው ጥቃት ዋናኛ አላማ የኢትዮጵያን ገጽታ ለማጠልሸት ያለመ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ገለጹ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከህዝብ ተወካዮች ለቀረቡ ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ አሸባሪው እና ቁማርተኛው ህወሃት የአለም ሀገራት ኢትዮጵያን ለመክሰስ ያስችላል በሚል ጥቃቱን መክፈቱን ገልጸዋል፡፡

በአፋር የተከፈተው ጥቃት የመላው ኢትዮጵያውን ጥቃት በመሆኑ በጋራ እንከላከለዋለንም ብለዋል፡፡
ለትግራይ ህዝብ ምግብ እና መድሃኒት አለመድረሱ ምንም ደንታ ያሌለው ህወሃት ዋነኛ ስሌቱ ያራሱ ጥቅም ብቻ ማስጠበቅ መሆኑን በግልጽ አሳይቷል ብለዋል፡፡

የአፋር እና የአማራ ህዝብ በወንድም ትግራይ ህዝብ ላይ መንገድ ለመዝጋት ቀርቶ የአሸባሪውን ህወሃት ቁስለኞችን በመንከባከብ ሞራል ያለው ህዝብ መሆናቸውን አሳይተዋል ብለዋል፡፡

በዚህ ጦርነት እንደ ትግራይ ክልል የደቀቀ ክልል የለም የሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ህዝብ ትግራይን መልሶ የመገንባት ዕዳ አለበት ብለዋል፡፡(EBC)

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰና የዓለም የምግብ ድርጅት የሥራ ሃላፊዎች ቦረና ዞንን እየጎበኙ ነው

የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰና የዓለም የምግብ ድርጅት የሥራ ሃላፊዎች ቦረና ዞንን እየጎበኙ ነው።
ልዑካን ቡድኑ በጉብኝታቸው ድርቁ ያስከተለውን ጉዳት እንደሚመለከቱ ይጠበቃል።

በቦረና ዞን ለተከታታይ ወቅቶች ዝናብ ባለመጣሉ የተከሰተው ድርቅ ቁጥሩ ከፍ ያለ የዞኑ ነዋሪን ለምግብ እህል እጥረት የዳረገ ሲሆን፥ በከብት ሀብት ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል።(ኤፍ ቢ ሲ)

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ምስጋና አቀረቡ

የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በህልውና ዘመቻው ወቅት በግንባር ዘምተው ላበረከቱት አስተዋጾ ምስጋና አቅርበዋል።

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄዎችን እያቀረቡ ያሉት የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄያቸው ከማቅረባቸው አስቀድመው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በህልውና ዘመቻው ወቅት ግንባር ዘምተው የአገር አንድነትን ለማስጠበቅ ለከፈሉት ዋጋ ምስጋና አቅርበዋል።

ብዙዎቻችን ኢትዮጵያን እንወዳለን እንላለን እርስዎም ይላሉ እርስዎ ግን በተጨባጭ ግንባር ዘምተው የአገር አንድነትን ያስጠበቁ ስለሆነ ምስጋና ይገባዎታል ሲሉም አባላቱ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ምስጋና አቅርበዋል።
በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄያቸውን እያቀረቡ ናቸው።

(ኢ ፕ ድ)

ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ “ለዓመቱ ምርጥ የአፍሪካ ወጣት” ሽልማት በእጩነት ቀረቡ

የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜ “በፊውቸር አፍሪካ የዓመቱ ምርጥ ወጣት” ሽልማት ውስጥ በእጩነት ቀረቡ።

አፍሪካውያን ወጣቶችን በማስተሳሰር የአህጉሪቷን ችግሮች ለመቅረፍ የሚንቀሳቀሰው “ዘ ፊውቸር አፍሪካ” ፕሮጀክት የ16ተኛውን ዘ ፊውቸር ሽልማት እጩዎችን ይፋ አድርጓል።

ታዋቂው የእግር ኳስ ተጫዋች ሞሐመድ ሳላህን ጨምሮ አምስት አፍሪካውያን በተካተቱበት የእጩዎች ዝርዝር ውስጥ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽነር ለሊሴ ነሜም ተካተዋል።

ለሽልማቱ በእጩነት መመረጣቸውን ተከትሎ ኮሚሽነሯ ባስተላለፉት መልዕክት “በሽልማቱ እጩ ዝርዝር ውስጥ በመካተቴ ከፍተኛ ደስታ ይሰማኛል፣ ለፕሮጀክቱም ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ብለዋል።

በእጩነት ከቀረቡት ውስጥ የዚምቧቡዌና የናይጄሪያ ስራ ፈጣሪዎችና ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ወጣቶች ይገኙበታል።

መቀመጫውን በሌጎስ ናይጄሪያ አድርጎ የሚንቀሳቀሰው “ዘ ፊውቸር አፍሪካ” አፍሪካውያን ወጣቶችን በማስተሳሰር በአፍሪካ አንገብጋቢ የሆኑትን የመልካም አስተዳደርና የስራ አጥነት ችግርን ለመፍታት እንደሚንቀሳቀስ መረጃዎች ያሳያሉ።

(ኢዜአ)

በሊባኖስ ያለሰነድ ይኖሩ የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ

በሊባኖስ ያለሰነድ ይኖሩ የነበሩ 80 ኢትዮጵያውያን ወደ አገራቸው ተመለሱ።

የኢፌዴሪ ቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤት ከሊባኖስ የኢሚግሬሽን መስሪያ ቤት ጋር በመነጋገር ነው በተለያየ ምክንያት ያለ ህጋዊ ሰነድ በሊባኖስ ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ያደረገው፡፡

ወደ ሀገራቸው የገቡት ዜጎች በ2014 ዓ.ም በጀት ዓመት በመጀመሪያ ዙር ተመዝግበው ከነበሩ መካከል 80ዎቹ መሆናቸውን ከቆንስላ ጄኔራል ጽህፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

(ኤፍ ቢ ሲ)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በቦረና ዞን ያለውን የድርቅ አደጋ ሁኔታ ለመመልከት ቦረና ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ያለውን የድርቅ አደጋ ሁኔታ ለመመልከት ቦረና ገብተዋል።

ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ቦረና ገብተዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመራው የልዑካን ቡድን የድርቅ አደጋ ጉዳት ያደረሰባቸውን የተለያዩ ቦታዎች ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ መስጠት የሚያስችል አቅጣጫ ይቀመጣል ተብሎ ይጠበቃል።

(ኤፍ ቢ ሲ)

የነዳጅ ስርጭትና አቅርቦቱ ላይ ምን አይነት ችግር አለመኖሩ ተገለጸ

የነዳጅ ስርጭት እና አቅርቦቱ ላይ ምን አይነት ችግር የለም ሲል የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት አስታወቀ።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ታደሰ ሀይለማሪያም ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት፥ ‘’ነዳጅ የለም’’ በሚል እየተናፈሰ ባለው ወሬ ተሽከርካሪዎች በማደያዎች ነዳጅ ለመቅዳት የሚያደርጉት ረዣዥም ሰልፎች ከእውነታው ጋር የተቃረነ ተግባር ነው።

አለ የሚባለው ችግር ለእኛም ግልጽ አይደለም ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ፥ የኢትዮጵያ ነዳጅ አቅራቢ ድርጅት የነዳጅ ስርጭት ጊዜውን ጠብቆ እያደረገ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ለአለብነትም ጥር 19 ቀን 2014 ዓ.ም በየቀኑ በአማካይ 2 ነጥብ 7 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ የተሰራጨ ሲሆን ፥ ትናንትና ብቻ 3 ሚሊየን ሊትር ነዳጅ ወደ ገበያ መሰራጨቱን አንስተዋል።

ሆኖም በየወሩ መጨረሻ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ጋር ተያይዞ ‘‘የዋጋ ልዩነት ይኖራል’’ በሚል ተሽከርካሪዎች በማደያዎች መሰለፋቸው ከዚህ ቀደም ከሚፈጠረው ሁኔታ መገመት ይቻላልም ነው ያሉት።
አንዳንድ አሽከርካሪዎችም በነዳጅ ማደያዎች ተሸከርካሪዎች በመሰለፋቸው ብቻ ነዳጅ የሌለ መስሏቸው የሚሰለፉ እንዳሉም ነው የጠቀሱት ዋና ስራ አስፈጻሚው።

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለስርጭት እየቀረበ ያለው ነዳጅ በመጠኑ እየጨመረ ከመምጣት ውጪ ቅናሽ የታየበት አይደለም ያሉትአቶ ታደሰ ፥ በመሆኑም ህብረተሰቡ በሚናፈሱ ወሬዎች ሊታለል አይገባም ብለዋል።

(ኤፍ ቢ ሲ)

ሚኒስቴሩ ከውጪ የሚገቡ የማዕድን ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት ከተመድ የቴክኒክ ድጋፍ ለማግኘት ተስማማ

የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ በኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ተወካይ ኦሬሊያ ፒ ካላብሮ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም ከውጪ የሚገቡ የማዕድን ምርቶችን በሀገር ውስጥ ለመተካት በሚሰሩ ስራዎች የቴክኒክ ድጋፍ ለማግኘት እና አቅም ግንባታ ላይ በጋራ ለመስራት መስማማታቸውን ሚኒስትሩ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ገልጸዋል፡፡

(ኤፍ ቢ ሲ)

ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከተማዋን በማስዋብ ለተሳተፉ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቀረቡ

የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ 35 ኛዉን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ መነሻ በማድረግ ከተማዋን በማስዋብ ለተሳተፉ ተቋማትና ግለሰቦች ምስጋና አቅርበዋል።

" 35 ኛዉን የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ መነሻ በማድረግ ከተማችንን እንድናሳምር እና እንድናስውብ ላቀረብንላችሁ ጥሪ በጎ ምላሽ በመስጠት ከተማችንን ዉብ ላደረጋችሁ ተቋማትና ግለሰቦች በራሴና በከተማ አስተዳደር ስም እጅግ አድርጌ ላመሰግናችሁ እወዳለሁ" ብለዋል።

(ኢ ፕ ድ)

የአፍሪካ ሕብረት 40ኛዉ የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ ዛሬ ይጀምራል

የአፍሪካ ሕብረት 40ኛዉ የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ የሕብረቱ አባል ሀገራት ሚኒስትሮችና የአህጉሩ ልዩ ልዩ ተቋማት ሀላፊዎች በሚገኙበት ዛሬ ይጀምራል።

በአርባኛው የስራ አስፈጻሚዎች ምክር ቤት ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የምስራቅና ደቡብዊ አፍሪካ አገራት የጋራ ገበያ (ኮሜሳ) ዋና ጸሀፊን ጨምሮ የህብረቱ አባል ሀገራት ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴታዎች አዲስ አበባ ገብተዋል።

የምክር ቤቱ ስብሰባ “የአፍሪካ አህጉርን የስርዓተ ምግብ አቅም መገንባት፣ የሰው ሃብት ልማት፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ልማትን ማፋጠን” በሚል የአፍሪካ ሕብረት ባዘጋጀው የ2022 መሪ ቃል ላይ የሚመክር ሲሆን ጥር 28 እና 29 ቀን 2014 ዓ.ም ለሚካሄደው 35ኛው የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ የሚቀርቡ ረቂቅ አጀንዳዎች ላይ ይወያያል ተብሎ ይጠበቃል።

የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት በሕብረቱ አባል አገራት የጋራ ፍላጎት የሆኑ የፖሊሲ ጉዳዮችን የሚያስተባብርና ውሳኔ የሚሰጥ ነው።

የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን አባላት በመምረጥ የሕብረቱ የመሪዎች ጉባኤ እንዲያጸድቅ የሚያደርግ ሲሆን ከቀጠናዊ የኢኮኖሚ ማህበረሰቦች፣ ከአፍሪካ ልማት ባንክ፣ ሌሎች የአፍሪካ ተቋማትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢኮኖሚ ኮሚሽን ያለው ትብብርና ትስስር እንዲጠናከር የማስተዋወቅ ስራ ያከናውናል።

የአፍሪካ ሕብረትና የአፍሪካ አጋሮች ያላቸውን ትብብር ማጠናከር የሚያስችሉ ፖሊሲዎችን በማዘጋጀት በአህጉሪቷ የሰላም፣ ጸጥታና ሌሎች የጋራ አጀንዳዎች ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቦችን ያቀርባል።

ምክር ቤቱ በአፍሪካ ሕብረት ስር የሚገኙ የተለያዩ ተቋማትን አፈጻጸምና ሕብረቱ እ.አ.አ በ2021 ያካሄዳቸውን ስብስባዎች የተመለ

አቶ አህመድ ሺዴ ከሳዑዲ አረቢያ የገንዘብ ሚኒስትር ጋር ተወያዩ

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ከሳዑዲ አረቢያ የገንዘብ ሚንስትር መሀመድ ቢን አብደላህ አል ጀዳን ጋር ተወያይተዋል::

በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ የተመራ እና ከመንግስት የስራ ሃላፊዎች እና የሃይማኖት ተቋማት መሪዎች የተውጣጣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ልዑካን ቡድን የሁለቱ ሃገራት ግንኙነት የበለጠ ስለሚጠናከርበት እንዲሁም በሳዑዲ ዓረቢያ የሚገኙ ዜጎች የአጭር ጊዜና ዘላቂ መፍትሄዎች ስለሚያገኙበት ሁኔታ ከከፍተኛ ባለስልጣናት ለመምከር አልሞ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ማቅናቱ ይታወሳል፡፡

ቡድኑ ባለፉት ቀናት በነበረው ቆይታ በሪያድ ከኢትዮጵያ ኮሙኒቲ አመራሮች እና አባላት፣ ከሀይማኖት መሪዎች እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰብ ጋር ተወያይቷል፡፡

ልዑኩም በትናንናው እለት በሳዑዲ አረቢያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረገ ሲሆን ÷በዛሬው ዕለት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሺዴ ከሳዑዲ አረቢያ አቻቸው መሀመድ ቢን አብደላህ አል ጀዳን ጋር መወያየታቸውን ከሳዑዲ አረቢያ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡(ኤፍ ቢ ሲ)

የውጭ ኩባንያዎች በማዕድን ዘርፍ በሚሳተፉበት መንገድ ላይ ውይይት ተደረገ

የማዕድን ሚኒስትር ኢንጂነር ታከለ ኡማ ከእንግሊዝ አምባሳደር አለስቴር ሜክፌል (ዶ/ር) እና ከአውስትራሊያ አምባሳደር ሚስ ጁሊያን ኒብሌት ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

ውይይቱም በማዕድንና በተፈጥሮ ጋዝ ፍለጋና ምርት ላይ በተሰማሩ የእንግሊዝ እና የአውስትራሊያ ኩባንያዎች የስራ እንቅስቃሴ ላይ ያተኮረ እንደነበር ተነግሯል፡፡

የእንግሊዝ እና የአውስትራሊያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የማዕድን ኢንቨስትመንት ላይ በሰፊው የሚሳተፉበት መንገድ ላይም ከአምባሳደሮቹ ጋር ውይይት ማድረጋቸውን ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው አጋርተዋል፡፡(EBC)

ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ 6 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ድጋፍ አደረገች

ፈረንሳይ ለኢትዮጵያ 6 ነጥብ 7 ሚሊየን ዶዝ የኮቪድ-19 ክትባት ድጋፍ አድርጋለች፡፡

ድጋፉን ኢትዮጵያ በኮቫክስ ጥምረት አማካኝነት በተያዘው ሳምንት መረከቧን በኢትዮጵያ ከፈረንሳይ ኤምባሲ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ድጋፉ ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ከፈረንሳይ የኮሮና ቫይረስ ክትባት ያገኘች ቀዳማ አገር ያደርጋታል፡፡(ኤፍ ቢ ሲ)