የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አጸደቀ
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለፌዴራል መንግሥት የ2014 በጀት ዐመት የቀረበለትን 122 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ በጀት አፀደቀ። በጀቱ በኢትዮጵያ በተከሰተው ጦርነት ተጨማሪ ወጪ በማስፈለጉ፤ የሚሰበሰበው ገቢ አሁን ያለውን የክፍያ ጥያቄ ለማስተናገድ አስቸጋሪ ሁኔታ በመፍጠሩ፤ እንዲሁም ወቅቱ የፈጠረውን የተጨማሪ ወጪ ፍላጎት በበጀት ሽግሽግ ለማስተናገድ ባለመቻሉ መቅረቡ ተገልጿል። ተጨማሪ በጀቱን በሀገር ውስጥ ብድር ለመሸፈን ታሳቢ መደረጉም ተነግራል። በዚህ መሰረት ለመከላከያ ለትጥቅ እና ቀለብ 90 ቢሊዮን ብር፣ ለዜጎች የዕለት የስንዴ እና አልሚ ምግብ ግዥ 8 ቢሊዮን ብር፣ በጦርነት የወደሙ መሠረተ ልማቶችን እና አገልግሎቶችን መልሶ የመገንባት ሥራ ለማስጀመር ከመንግሥት ግምጃ ቤት 5 ቢሊዮን ብር ተደግፎ መቅረቡ ተገልጿል። ለመልሶ ግንባታ የተመደበው ገንዘብ አንሷል የሚሉ ጥያቄዎች ከምክር ቤት አባላት በስፋት ተጠይቋል። የገንዘብ ሚኒስቴር፦ ገንዘቡ ሥራውን ለማስጀመር እንጂ በቂ ነው የሚል አቋም እንደሌለ፤ ሆኖም በሂደት የመልሶ ግንባታ ተግባሩ በልዩ ልዩ አሠራር ታግዞ እንደሚከናወን ምላሽ ሰጥቷል። የተጨማሪ በጀትና የወጪ አሸፋፈን ማስተካከያው በዘጠኝ ተቃውሞ፣ በሰባት ድምፅ ተአቅቦ በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል።
ዘገባ፦ ሰለሞን ሙጬ ዶይቸ ቬለ (DW) አዲስ አበባ